👁 የምታይበት መንገድ

 áŠ áŠ•á‹ľáŠ• የናጠጠ ሀብታም ቤተሰብ የሚያስተዳድር አባት ልጁ ሾለ ድኽነት እንዲያውቅ ስለፈለገ በከተማው ጥግ ወዳለው የድኾች መንደር ልጁን ይዞት ይሄዳል፡፡ እዚያም ወደ አንድ ድኻ ቤት ይገባና ለልጁ ሁሉንም ነገር ያሳየዋል፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባትና ልጅ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቤታቸው በመኪናቸው ይመለሳሉ፡፡ አባትም ልጁን ‹‹ጉዞው እንዴት ነበር?›› ይለዋል፡፡

ልጁም ‹በጣም ጥሩ ነበር›› ብሎ ይመልስለታል

አባትዬውም ‹‹ድኾች ምን ዓይነት እንደሆኑ አየህን?›› ይለዋል፡፡

ልጁም ‹‹በርግጠኛነት አይቻለሁ›› ሲል መለሰለት፡፡

‹‹ታድያ ምን ተማርክ?›› አለው አባት፡፡

‹እኛ አንድ ውሻ አለን፤ እነርሱ ግን አራት ውሻ አላቸው፡፡ እኛ እስከ ግቢያችን ግማሽ የሚደርስ መዋኛ አለን፤ እነርሱ ግን ማለቂያ የሌለው ሐይቅ አላቸው፡፡ እኛ በግቢያችን ውስጥ ከእንጨት የተሠሩ በጎች አሉን፤ እነርሱ ግን በሕይወት ያሉ ብዙ በጎች አሏቸው፡፡ እኛ የገዛናቸው ጥቂት አምፖሎች በቤታችን አሉን፤ እነርሱ ግን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ከዋክብት አሏቸው፡፡ የእኛ የፊት ለፊት ሜዳ ትንሽ ናት፤ እነርሱ ግን የማይጠገብ መስክ አላቸው፡፡ እኔ መጫወት የምችለው በግቢዬ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ግን እስከ ሐይቁ ድረስ ባለው ሜዳ ይንቧረቃሉ፡፡››

አባትዬው አፉን በመዳፉ ይዞ ነበር የሚሰማው፡፡

በመጨረሻም ልጁ ‹‹ አባዬ እኛ ምን ያህል ድኻ እንደሆንን ስላሳየኸኝ አመሰግንሃለሁ›› አለው፡፡

በማንኛውም ነገር ወሳኙ ነገሩን እንዴት ታየዋለህ? ነው፡፡ ለአንዱ የሞት ምክንያት የሚሆነው ለሌላው የመዳን ምክንያት ይሆናል፡፡ ለአንዱ ተስፋ የሚያስቆርጠው ለሌላው ተስፋ ይሰጠዋል፡፡ አንዱን የሚያተርፈው ሌላውን ያከስረዋል፡፡ አንዳንዶቹ የሚስማሙበት፣ ሌሎቹን ይለያያቸዋል፡፡ ለአንዱ ሀብት፣ ለሌላው ድኽነት ነው፡፡ ለአንዱ እጅግ ውብ የሆነው፣ ለሌላው መልከ ጥፉ ነው፡፡ ለአንዱ ጠባየ መልካም የሆነው፣ ለሌላው አብረውት ሊኖሩት የማይቻል ነው፡፡ አንዱ ለጋብቻ የሚመርጠውን ሌላው ለደቂቃ ቡና አብሮት ሊጠጣ አይፈልግም፡፡

የእነዚህ ነገሮች አንደኛው ምክንያት ነገሩን የምናይበት መንገድ ነው፡፡ አንድን ነገር በችግር ዓይንም ሆነ በመፍትሔ ዓይን ማየት ይቻላል፡፡

በ17ኛው መክዘ ከተነሡት እንስት ኢትዮጵያውያን ቅዱሳት መካከል አንዷ የሆነችው ወለተ ጴጥሮስ ከንጉሥ ሱስንዮስ ጋር ተጋጭታ ወደ ዋልድባ ገብታ ነበር፡፡ እዚያ እርስዋ በገባችበት የሴቶች ገዳም ውስጥ የነበረች አንዲት አሮጊት ነበረች፡፡ ይህች ሴት ጠባይዋ እጅግ አስቸጋሪ ነበር ይባላል፡፡ ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢደረግላት ትራገማለች እንጂ አታመሰግንም፡፡ የሚያገለግሏትንም ሁሉ ትነዛነዛለች፡፡ አንዳንዴም ትማታለች፡፡

ወለተ ጴጥሮስ ምክንያቱን ስትጠይቅ የሴትዮዋን የጠባይ ክፋት ነገሯት፡፡ እርስዋም ይህንን ስትሰማ ‹‹እኔ አገለግላታለሁ›› ብላ ወደ ሴትዮዋ ሄደች፡፡ እጅግ የንትወዳትና የምታከብራት ጓደኛዋ እኅተ ክርስቶስ እንኳን በውሳኔዋ ተገርም ሃሳቧን እንድትለውጥ ስትነግራት ፈቃደኛ አልሆነችም ነበር፡፡

ለሴትዮዋ ትታዘዛለች፣ ምግብ ታበስላለች፣ ቤቷን ትጠርጋለች፣ ሰውነቷን ታጥባለች፣ ትላላካታለች፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስዳታለች፡፡ ይህንን ሁሉ ብታደርግላትም ግን ሴትዮዋ አትደሰትም ነበር፡፡ ታማርራለች፤ ትራገማለች፤ ትሳደባለች፤ ትተቻለች፤ ታናቋሽሻለች፤ ከዚያ የባሰም ሲመጣ ትማታለች፡፡ አንድ ቀን እንዲያውም ወለተ ጴጥሮስ ለእርስዋ ምግብ እየሠራች እያለ ከምድጃው እሳት የያዘ እንጨት አውጥታ በፍሙ መትታት ነበር፡፡

ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ግን አንዲትም ቀን አማርራ አታውቅም ነበር፡፡ ነገሩንም ሁሉ በምስጋና ትቀበለው ነበር፡፡ ይህ ነገርዋም ስትሰድባትና ስታማርራት ለሚሰሙት ሌሎች እኅቶች ግራ ይገባቸው ነበር፡፡ ‹‹ለምን አትተያትም? ምን ትጠቅምሻለች? እንዲህ ከምትረግምሽ ሴት ምን በረከት ይገኛል›› ይሏት ነበር፡፡ እርስዋ ግን መልስ ሰጥታቸው አታውቅም፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገለቻት በኋላ ሴትዮዋ ሞተች፡፡ ወለተ ጴጥሮስም እጅግ አዝናና አልቅሳ ቀበረቻት፡፡ የደረሰባትን ሁሉ የሚያውቁት እኅቶችም እንደዚያ በማልቀስዋ ተገረሙ፡፡ አንድ ቀንም እንዲህ ብለው ጠየቁዋት ‹‹ለመሆኑ ምን አድርጋልሽ ነው አብረሻት የኖርሽው? ከእርስዋስ ምን አገኘሽ? ደግሞስ ምን ጎድሎብሽ ነው በመሞቷ ያለቀስሽው?››

ወለተ ጴጥሮስም እንዲህ አለቻቸው ‹‹ንብ ታውቃላችሁ? ንብ መልከ ጥፉና ክፉ ናት፡፡ መርዟም ሰው ከነደፈ ይጎዳል፡፡ ያምማል፡፡ አንዳንዴም ለመሞት ያደርሳል፡፡ ማንም የንብን ጠባይ አይወደውም፡፡ ከንብ ይልቅ ዝንብ ጠባይዋ መልካም ነው፡፡ አትናደፍም፤ መርዝ የላትም፤ አትጎዳም፤ በመርዟም ለሞት አታደርስም፡፡ ዝንብን የንብ ያህል ማንም አይፈራትም፡፡ ግን ዝንብ ማር አትሠራም፡፡ ለዝንብ ማንም ቀፎ አይሠራላትም፡፡ ምክንያቱም ማር የላትምና፡፡ ሰው ሁሉ የንብን ጠባይዋን ታግሦ፣ መርዟንም ተከላክሎ ለማርዋ ሲል አብሯት ይኖራል፡፡ ማንም ስለ ንብ ክፋትን መርዝ አያስብም፤ ስለ ማርዋ ነው እንጂ፡፡

‹‹እኔም እንደዚያው ነው፡፡ ይህች ባልቴት ጠባይዋ ክፉ ነው፡፡ ነገር ግን ከእርስዋ ዘንድ እንደ ማር የሚገኝ ብዙ በረከት አለ፡፡ ንብ ሌላውን የምትጠቅመውን ያህል ለራስዋ አትጠቀምም፤ ይህችም ሴት እኔን የጠቀመችኝን ያህል ራስዋን አልጠቀመችም፡፡ እዚያ ቤት ብዙ ነገር አጋኝቻለሁ፡፡ ጠባይዋን ታግሼ፣ መርዝዋንም ተከላክዬ ብዙ ማር ቆርጫለሁ፡፡ እናንተ መናደፏንና መርዟን ብቻ ነው የምታዩት፡፡ ማርዋ ሊታያችሁ አልቻለም፡፡ እኔ ደግሞ ማሩ እንጂ መናደፏ አልታየኝም፡፡›› አለቻቸው፡፡

የምታይበት መንገድ የምትደርስበትን ግብ፣ የምታገኘውን ነገር፣ የምታመጣውን ውጤት፣ የምታተርፈውን ትርፍ፣ የምታፈራውን ወዳጅ፣ ይወስነዋል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደጻፈው

Comments